ይፋት ልማት ማህበር/ይልማ በኢትዮጵያ ፣አማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን ይፋትን መሰረት አድርጎ ከጣር ማበር እስከ አንፃኪያ ድረስ ያሉ አከባቢዎችን አካቶ ልማትና እድገት ለማፋጠን ታስቦ ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት ጀምሮ ጥረት ሲደረግ የቆየ እና ነፃ ሆኖ ከመቋቋም አንፃር ሁኔታዎች ሳይፈቅዱ ቆይቶ ቁጭትን መሰረት አድርጎ እና በይፋት ምሳሌያዊ እድገት ማምጣትን ዓልሞ በ250 በላይ አባላት ተመስርቶ በኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 አንቀጽ 57/1 መሰረት በኤጀንሲው ምዝገባ ሰርተፊኬት ቁጥር 5332 አገር በቀል ድርጅት ሆኖ የተቋቋመና የተመዘገበ ማህበር ፡፡
ይልማ እንደ ሲቪክ ማህበር ከሁሉም አጋር አካሎች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ዉስጥ የራሱ በግልፅ የተቀመጠ ዓላማዎች ያስቀመጠ በእቅድና በፕሮግራም ለመስርት እየተጣጣረ የሚገኝ ማህበር ነዉ፡፡ እንደአጋጣሚም ማህበራችን ተደራጅቶ ገና ስራ እንደጀመረ አጣዬና አካባቢዉ ከፍተኛ አደጋ ዉስጥ በመግባቱ ይህንን መሰረት አድርገን በአስቸኳይ ከህዝቡ ጎን ለመቆም በመወሰን፣ አባላትን እና አጋሮችን በማስተባበር ከህዝቡ ጎን በመቆም የእለት ደራሽ እርዳታ ቀድሞ በማቅረብ አለኝታ እና ድምፅ በመሆንም ሃላፊነትን መዉሰድ የቻለ እንዲሁም በህዝቡ ተቀባይነትን ያገኘ ማህበር ነዉ፡፡
ማህበራችን ሃሳቡም፣ ዓላመዉም ፣የተግባር ጅምሩም በእቅድ ተሰናስሎ በቀጣይ ጊዜ በግብርናና ተፈጥሮ ሃብት፣ በትምህርት፣ በጤና ፣ በመልካም አስተዳርና መሰረተ ልማት ዘርፎችን አቀናጅቶ በማቀድና በመተግበር የአካባቢዉን ገፅታ በመገንባት የህብረተሰቡን ህይወት በማሻሻል በግልፅ የሚታይ አይነታዊ ለዉጥ ለማምጣት እየሰራ ሲሆን በተለይ ስትራቴጂክ እና ዓመታዊ እቅድ በማዘጋጀት ሂደት ላይ ስንሆን ይህንኑ መሰረት አድርጎ ከአጋሮች ጋር ተቀራርበን በላቀ ደረጃ ለመስራት እየተንቀሳቀስን ነዉ ፡፡
ያሰብነዉ እና እየተጣጣርነበት ያለዉ ጅምር እንዲሳካ መላ አባለት፣ አጋር አካላት በተለይም የዉጪና ሃገር ዉስጥ ረጂ ድርጅቶች፣ የምርምር ተቋማት፣ ዩንቨርስቲዎችና ኢምባሲዎች እንዲሁም ህብረተሰቡና የመንግስት አካላት ሁሉ ኢትዮጵያን በመገንባትና በማሳደግ ዉስጥ እንዳንዱን አካባቢ እንደየሁኔታ እንዲለማ መስራት ጠቃሚ ነዉና ከእቅድ ጀምሮ አጋርነትን መስርተን በጋራ መስራት የምንፈልግ ስለሆነ ሁሉም አካል ከእኛ ጋር ተቀራርበን በትብብር እንድንሰራ ጥሪዬን አቀርባለሁ ፡፡
በጋራ የሰላምና ልማት ተምሳሌት ይፋትን እንገነባለን !
መስፍን ተፈራ
የይልማ ስ/ኮሚቴ ሰብሳቢ