“ልማት ድንበር የለውም፤ ልማት የኹላችንም አንድነት እና መደጋገፍ ይጠይቃል” ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባሕር ዳር፡ ግንቦት 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ ከተማ በሚገነባው የአማራ ባሕል ማእከል ግንባታ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የማእከሉ ግንባታ የሚያርፍበትን ካርታ ለአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር አስረክበዋል፡፡ “ልማት ድንበር የለውም፤ ልማት የኹላችንም አንድነት እና መደጋገፍ ይጠይቃል” ያሉት ምክትል ከንቲባ አዳነች በተለያዩ ስያሜ የተደራጁ የልማት ተቋማት ከሚሞሉት የመሰረተ ልማት ክፍተት በላይ ለአብሮነታችን ዋልታ ናቸው ብለዋል፡፡ “ሽህ ሆነን እንደ አንድ፤ አንድ ሆነን እንደ ሽህ” የሚለው የአልማ መልዕክትም ለአብሮነታችን መቆሙን ያመላክታል ነው ያሉት ከንቲባዋ፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚሠሩ የልማት ተቋማት ተቀራርበው እንዲሠሩ፣ ሕዝቦቻቸውን እንዲያቀራርቡ እና በጋራ የሀገር ግንባታ ሂደት ጉልበት እንዲሆኑ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ከሚያለያዩን ውስን ጉዳዮች ይልቅ አንድ በሚያደርጉን እልፍ ጉዳዮቻችን ላይ በጋራ እንሠራለን ነው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፡፡ አዲስ አበባንም የኢትዮጵያዊያን የልማት እና የቱሪዝም ማእከል ለማድረግ ይሠራል ብለዋል፡፡